መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው ትምህርት ሂደት በተጓዳኝ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተማር ጀመረ

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው ትምህርት ሂደት በተጓዳኝ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከፍቶ ማስተማር ጀመረ
=====
መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛው ትምህርት ሂደት በተጓዳኝ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመክፈት ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀመረ ።

ዩኒቨርሲቲው በልዩ ትምህርት ቤቱ ማስተማር የጀመረው በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያላቸው ዘጠነኛ ክፍል የሆኑ 80 ተማሪዎችን ዘንድሮ አወዳድሮ በመቀበል ነው።

በልዩ ትምህርት ቤቱ የመማር ዕድል ያገኙት ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ በትምህርት ቤቱ እርስ በርስ በመረዳዳትና ዕውቀትን በመጋራት ብቁ ሆነው እንዲወጡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቱ የዘነጠኛ ክፍል ተማሪ ሂክማ ጁንዲ፤ “ትምህርት ቤቱ ሰፋ ባለ መልኩ እውቀት ለመገብየት ዕድል ይፈጥራል” ብላለች።

” በትምህርት ቤት ቆይታችን የሚባክን ጊዜ እንዳይኖር በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እጥራለሁ” ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሃዋ አህመድ ናት።

ሌላኛው የዘነጠኛ ክፍል ተማሪ አህመድ ሁሴን ፤የትምህርት ቤቱ ከቤተሰባቸው ሳይርቁ ጥራት ያለው ትምህርት ለመማር ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግሯል።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አህመድ ከሊል(ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት ዘርፍ ያገጠመውን ሥብራት ለመጠገን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለማቃለል መንግሥት በትምህር ዘርፍ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ “ኢኒሼቲቮች” እንዲሳኩ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በመደበኛነት እያከናወነ ከሚገኛው የትምህርት ሂደት በተጓዳኝ በአዲስ መልኩ ሥራ ያስጀመረው ልዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍሉ የሆኑ 80 ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ተቀብሎ የመማር ማስተማሩን ሥራ መጀመሩን ታውቋል።

” ተማሪዎቹ በቴክኖሎጂና ፈጠራ የበለጸጉና ክህሎታቸው የላቀ እንዲሆን እንደሚሰሩ የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ አለማየሁ ገዘኽኝ ናቸው።

ተማሪዎች በትምህርታቸው ብቁና በሥነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ትምህርት ቤቱ በተለይም 2017 የትምህርት ዘመን መንግሥት በተማሪዎች ውጤታማነት ዙሪያ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት አዳዲስ ብቃት ያላቸውን መምህራንን ቀጥሮ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።