መንግስት የጤና አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ነው- ዶክተር ደረጄ ዱጉማ
======
መንግስት የጤና አገልግሎትን ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ አስታወቁ።
የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ዛሬ በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በመገኘት አዳዲስ የህክምና አገልግቶችን በማስጀመር የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡
“ሲቲ ስካን፣ ላፓራስኮፒና ፓቶሎጂ ላብራቶሪ” በሆስፒታሉ አዲስ የተጀመሩ አገልግሎቶች ናቸው ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ ከልዩ ልዩ ባድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው፡፡
መሰረተ ልማትና አቅርቦትን ማጠናከር ለጤናው ዘርፍ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለጤናው ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል አስፈላጊ መሆናቸውን በመረዳት እየተሰራበት መሆኑን አስረድተል፡፡
በጎባ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት የጀመሩት ዘመናዊና አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶች የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡
በተለይ የሲቲ ስካንና ላፓራስኮፒ ማሽኖች ሥራ መጀመራቸው ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ መሃል አገር ይደረግ የነበረውን ጉዞ እንደሚያስቀር ጠቅሰዋል፡፡
ሆስፒታሉ አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶችን ከማስጀመር በተጓዳኝ እያስገነባ የሚገኘው ባለ ስምንት ወለል ህንጻ የአካባቢውን የህክምና አገልግሎት ማሻሻል ብቻ ሳይሆን የአጎራባች ዞኖች የጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ረገድ የሚያበረክተው ድርሻ የላቃ መሆኑን አክለዋል፡፡
እየተጠናቀቀ የሚገኘው አዲሱን የሆስፒታል ህንጻን በህክምና ቁሳቁስ ለማሟላት በሚደረገው ጥረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሉ ጤና ቢሮና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማሟለት የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡
“የህክምና ተቋማትን በቁሳቁስ ማሟላትና የሚሰጡትን አገልግሎቶቹን ማሻሻል ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቦኮና ጉታ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት የህብረተሰቡን መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ቢሮው በተለይ በክልሉ ያሉ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል በበኩላቸው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝምና በተፈጥሮ ጥበቃ ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለመሆን አቅዶ እየሰረ ነው ፡፡
በተለይ በዩኒቨርሲቲው ሥር የሚተዳደረው የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል በጤናው መስክ የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ በተጓዳኝ የመማር ማስተማርና የምርምር ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ሆስፒታሉ የጀመራቸው አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶች በአካባቢው ለሚገኙ ታካሚዎች ብቻ ሳይሆን በዩኒቨርሲቲው ለሚካሄዱ የመማር፣ ማስተማርና የምርምር ሥራዎችን ለማሳለጥ አጋዥ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
የጎባ ሪፈራል ሆስፒታል ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን መሠረታዊ የህክምና አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጄይላን ቃሲም ናቸው፡፡
“ሆስፒታሉ በአዲስ መልኩ ያስጀመራቸው የሲቲስካን፣ ላፓራስኮፒ የምግብ መውረጃ ቱቦ ህክምና፣ የጨጓራ ካንሰርና ሌሎች በሽታዎች ምርመራና የህክምና አገልግሎቶች የሆስፒታሉን የህክምና አገልግሎት አንድ እርምጃ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው” ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ አዳዲስ የተጀመሩ የህክምና አገልግቶሎች ላይ የሆስፒታሉ “ባለሙያዎች እስከ ውጭ አገር ድረስ ስልጠና የወሰዱ በመሆናቸው ሥራውን ቀጣይና ውጤታማ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡
ሮቤ፤ የካቲት 24ቀን 2016(ኢዜአ)፦